“በመጀመሪያ ጠቅላይ ሚንስትሩ ፣ እኛን ለማየተ በመምጣትዎ ፣ እግዚአብሔር ይስጥዎ! እግዚአብሔር ይስጥዎ! እግዚአብሔር ይስጥዎ!”
ጠ/ሚንስትሩም እንደማፈር ብለው ፤ በተሰጣቸው ምርቃት ደስ እንዳላቸው ለማሳየት ቢስቁ ክብራቸው ሊቀንስ ሆነና ፣ የታፈነች ሳቅ ጉንጫቸው ላይ አዝለው ፤ በአንገታቸው የይቀጥሉ ምልክት ሰጡ ። ሰውየውም ቀጠሉ ፤
“ጌታዬ! እኔ የምለው እኛ የምንኖረው ብዙም ቆሻሻ በማይታይበት ፣ ሠላማዊ ፍሰት ባለበት ሠፈር ከሆነ ፣ አሁን ፍሰታችን በቤት መሆን አለበት? ነው ወይስ እንደለመድነው በሠላም ቦዩን ይዘን ብንቀጥል ነው የሚስሻለው? ይህ ነው ጥያቄዬ ክቡርነትዎ ።” ካሉ በኋላ ጥድፍ ብለው ወንበራቸው ላይ ተቀመጡ ።
ጠ/ሚንስትሩም ጉሮሯቸውን በዉሃ አርጥበው ፤ የጉዳዩ ድግግሞሽ ትንሽ እየሰለቻቸው መሆኑ እንዳይታወቅባቸው አንገታቸዉን ዘቅዘቅ አርገው ፤
“አመሰግናለሁ አባቴ ፣ ለጠየቁት ጥያቄ ። ሰፈሮት ሠላም መሆኑ የሚያስመሰግን ነው ። ሌሎች ሠፈሮችም እናንተ ያላችሁበት ደረጃ እንዲደርሱ ነው ጥረታችን ። ነገር ግን አንዱን ከአንዱ መነጠል ጥሩ ስለማይሆን ፣ የእርሶም ሠፈር ባለበት እንዲዘልቅ ፣ የተሻለው አማራጭ የቤት ፍሰት በቤት መሆኑ ስለሆነ ሁሉም ሠፈር ይህን ተግባራዊ ማድረግ አለበት ፡፡ የግል ፍሰት በግል ። የጋራ ፍሰት በጋራ ። የጋራ ፍሰት የሚመጣው ከተፈጥሮ ነው ። ከዝናብ ፣ ጎርፍ እና መሰል ነገሮች ውጪ” ብለው በእንጥልጥል ትተውት ወደ ሚቀጥለው ነጥብ ሊሻገሩ ሲሉ ፤ ከነጠላቸው ዉስጥ መኖር እና አለመኖራቸው የሚያጠራጥር ወይዘሮ እጃቸውን እያወጡ ተነሱ ። ጠ/ሚንስትሩም ዓይን ለዓይን መገጣጠማቸውን ላለመካድ ዕድል ሠጧቸው ።
“አመሰግናለሁ ጠ/ሚንስትሩ ። እንደው አባም ያሉት ምርቃት እጥፍ ድርብ ሆኖ ይድረስዎ! እንደው እርስዎ ከመጡ በኋላ እኔ እንደው ልጅነት ነው የተሰማኝ ። ታዲያ ያለኝ ጥያቄ አንዳንዶቻችን ልብስ በማጠብ የምንተዳደር ነን ። እንደው ውሃ ቀድተን ስንሄድ ስንመለስ የምናፈሰው ፤ ግቢ ለሌላቸው ልብስ አጥበን የምንደፋው እዛችዉ መሬቷ ላይ ነው ፤ ፀሀዩዋ እንድታደርቃት ብለን ። ታዲያ አሁን እኛ እንደምን ነው የምንሆነው?”
ጠ/ሚንስትሩም ያልጠበቁት ጥያቄ በመሆኑ በስጨት ቢሉም ፣ ፖሊሲ ፖሊሲ ነዉና ፣ ፊታቸውን ኮስተር አድርገው ፣
“አመሰግናለሁ እናቴ ። ጥያቄዎ ትክክል ነው ። እነዚህን ነጥቦች ያው በሂደት የምናያቸው ናቸው ። ለአሁን ግን እናንተ ትችላላቹ ፤ እናንተ አትችሉም ማለቱ ሀሳቡን የሚነጣጥለው እንዲሁም ኢ-ዲሞክራሲያዊ ስለሚሆን ፤ ሙያቹ ውሃ መድፋት የሚያካትት ነዋሪዎች በተቻለ አቅመ በቀጣሪዎቻቹ ግቢ ውስጥ ፍሰቱን ማስቀረት አለባቹ ። ውሃ ሲያመላልሱ ማፍሰሱ ከፖሊሲም በላይ የውሃ ብክነት ስለሆነ ጄሪካኑንም ቢሆን በደንብ ማጥበቅ ፤ ቧንቧዉን አጥብቆ መዝጋት ከእናንተ ይጠበቃል ።” ካሉ በኋላ ወደ አጀንዳ ሁለት ለመግባት ማንንም አላይም ፣ አልሰማም ብለው ወረቀታቸው ላይ ተቀረቀሩ ። ይሁን እንጂ አንድ ሙሉ ልጅነቱን አቁማዳ ውስጥ ያሳለፈ የሚመስል ወጠምሻ ድምፁን ከፍ አድርጎ ማንባረቅ ጀመረ፤
“ጠ/ሚንስትር ! ”
እድምተኛው በሙሉ በትዝብት አፈጠጠበት ።
“ጠ/ሚንስትር ፣ እንዴት ነው ፍሰት በቤት ውስጥ ይሁን የምትሉት? እኛ ኳስ ሜዳ ሄደን እንጫወታለን ። ለምሳሌ እሁድ እሁድ ከጠዋት ከ ፩ እስክ ፫ - ፬ ሠዐት ፍልሚያ ነው ። ብርም ይመደብበታል ። ከተፋለምን በኋላ የአንዳንዶቻችን ቤት ሩቅ ስለሆነ ትንሽ ውሀ ከሠፈር ለማምነን ፤ ሜዳው ዳር ለቅለቅ ብለን ነው የምንበተነው ። እንዴት ነው ታዲያ ፍሰት ይቁም የሚሉት ጠ/ሚንስትር ? የኛስ ኳስ?”
ጠ/ሚንስትሩ የታዳሚው የፍሰት አባዜ በቀላሉ የማይፈታ መሆኑ ገብቷቸው ፤ ሩብ ላይ የተውትን ውሃ ተጎንጭተው ፤ ተስፋ በቆረጠ አንደበት ፣
“እነዚህን ሁሉ ጥያቄዎች በአካባቢያቹ ባሉት ቀበሌ ጽ/ቤቶች የሚስተናገዱ ይሆናል ። ልክ ነው ፤ የሁሉም ነዋሪ ህይወት በቀመር ይለያያል ። የምናወጣው ፓሊሲ የጋራ እንደመሆኑ መጠን የሚያስከትለው ተጽዕኖ አዳመጦ መልስ መስጠት የኛ ድርሻ ነው ። ስብሰባው ወደ ፊት እንዲሄድ እና ያልዳሰስናቸዉን ነጥቦች እንድናስተናግድ ለአሁን በቀበሌ ቅሬታችሁን አስመዝግቡ።”
⦿
በወሩ ጠ/ሚንስትሩ ከስብሰባው ቀሩ ። እንጥላቸው ወርዷል ተባለ፡፡
“ለምን ወረደ? እናንተ አትንከቧከቧቸውም እንዴ?” በማለት እድምኞቹ በቁጣ እየተንጫጩ እና እየተራገሙ ስብሰባው ሳይጀመር ጥለውት ሄዱ ።
⦿
ጠ/ሚንስትሩም የሆነውን ሲሰሙ ፣ ከእንጥል መውረድ ወደ ድካም ፣ ከድካም ወደ ንጭንጭ ፣ ከንጭንጭ ወደ እርጅና ተሻግረው ፤ እድሜቸው ሳያጥር አጥሮ ፤ የሠፈሩ መንገዶች ውሃ ለዕለት ሳያጡ ፤ የሀገሬው ህዝብ በነቂስ ወቶ ፤ እሪታ እና ዋይታ በተደበላለቀበት ቀትር ፣ ከደረቅ መሬት ተቀበሩ።⦿
እ.እ.አ ፳/፯/፳፻፲፱ በቦስተን፣ ማሳቹስት፣ የተባበሩት አሜሪካ መንግስታት ተጻፈ
© ፳፻፲፰ ማሳሙኔ በላይ (ብርሃኑ ታደሰ ገሰሰ)። መብቱ በህግ የተጠበቀ ነው።
በዚህ ላይ የቀረቡት ስራዎች በሙሉ የደራሲው የመጀመሪያ የፈጠራ ውጤቶች ናቸው። ከደራሲው የጽሁፍ ፈቃድ ውጪ ማንኛውንም ስራ ማባዛት፣ ማሰራጨት ወይም ማሻሻል በጥብቅ የተከለከለ ነው። ለህትመት ፈቃድ ወይም ለሌሎች ጥያቄዎች በ masamunebelay@outlook.com ያግኙን።