“በመጀመሪያ ክቡር ከንቲባችን፣ እኛን ለማየተ በመምጣትዎ ፣ እግዚአብሔር ይስጥዎ! እግዚአብሔር ይስጥዎ! እግዚአብሔር ይስጥዎ!”
ከንቲባው እንደማፈር ብለው ፤ በተሰጣቸው ምርቃት ደስ እንዳላቸው ለማሳየት ቢስቁ ክብራቸው ሊቀንስ ሆነና ፣ የታፈነች ሳቅ ጉንጫቸው ላይ አዝለው ፤ በአንገታቸው የይቀጥሉ ምልክት ሰጡ ። ሰውየውም ቀጠሉ ፤
“ጌታዬ! እኔ የምለው እኛ የምንኖረው ብዙም ቆሻሻ በማይታይበት ፣ ሠላማዊ ፍሰት ባለበት ሠፈር ከሆነ ፣ አሁን ፍሰታችን በቤት መሆን አለበት? ነው ወይስ እንደለመድነው በሠላም ቦዩን ይዘን ብንቀጥል ነው የሚስሻለው? ይህ ነው ጥያቄዬ ክቡርነትዎ ።” ካሉ በኋላ ጥድፍ ብለው ወንበራቸው ላይ ተቀመጡ ።
ከንቲባው ጉሮሯቸውን በዉሃ አርጥበው ፤ የጉዳዩ ድግግሞሽ ትንሽ እየሰለቻቸው መሆኑ እንዳይታወቅባቸው አንገታቸዉን ዘቅዘቅ አርገው ፤
“አመሰግናለሁ አባቴ ፣ ለጠየቁት ጥያቄ ። ሰፈሮት ሠላም መሆኑ የሚያስመሰግን ነው ። ሌሎች ሠፈሮችም እናንተ ያላችሁበት ደረጃ እንዲደርሱ ነው ጥረታችን ። ነገር ግን አንዱን ከአንዱ መነጠል ጥሩ ስለማይሆን ፣ የእርሶም ሠፈር ባለበት እንዲዘልቅ ፣ የተሻለው አማራጭ የቤት ፍሰት በቤት መሆኑ ስለሆነ ሁሉም ሠፈር ይህን ተግባራዊ ማድረግ አለበት ፡፡ የግል ፍሰት በግል ። የጋራ ፍሰት በጋራ ። የጋራ ፍሰት የሚመጣው ከተፈጥሮ ነው ። ከዝናብ ፣ ጎርፍ እና መሰል ነገሮች ውጪ” ብለው በእንጥልጥል ትተውት ወደ ሚቀጥለው ነጥብ ሊሻገሩ ሲሉ ፤ ከነጠላቸው ዉስጥ መኖር እና አለመኖራቸው የሚያጠራጥር ወይዘሮ እጃቸውን እያወጡ ተነሱ ። ከንቲባው ዓይን ለዓይን መገጣጠማቸውን ላለመካድ ዕድል ሠጧቸው ።
“አመሰግናለሁ ክቡር ከንቲባው። እንደው አባም ያሉት ምርቃት እጥፍ ድርብ ሆኖ ይድረስዎ! እንደው እርስዎ ከመጡ በኋላ እኔ እንደው ልጅነት ነው የተሰማኝ ። ታዲያ ያለኝ ጥያቄ አንዳንዶቻችን ልብስ በማጠብ የምንተዳደር ነን ። እንደው ውሃ ቀድተን ስንሄድ ስንመለስ የምናፈሰው ፤ ግቢ ለሌላቸው ልብስ አጥበን የምንደፋው እዛችዉ መሬቷ ላይ ነው ፤ ፀሀዩዋ እንድታደርቃት ብለን ። ታዲያ አሁን እኛ እንደምን ነው የምንሆነው?”
ከንቲባው ያልጠበቁት ጥያቄ በመሆኑ በስጨት ቢሉም ፣ ፖሊሲ ፖሊሲ ነዉና ፣ ፊታቸውን ኮስተር አድርገው ፣
“አመሰግናለሁ እናቴ ። ጥያቄዎ ትክክል ነው ። እነዚህን ነጥቦች ያው በሂደት የምናያቸው ናቸው ። ለአሁን ግን እናንተ ትችላላቹ ፤ እናንተ አትችሉም ማለቱ ሀሳቡን የሚነጣጥለው እንዲሁም ኢ-ዲሞክራሲያዊ ስለሚሆን ፤ ሙያቹ ውሃ መድፋት የሚያካትት ነዋሪዎች በተቻለ አቅመ በቀጣሪዎቻቹ ግቢ ውስጥ ፍሰቱን ማስቀረት አለባቹ ። ውሃ ሲያመላልሱ ማፍሰሱ ከፖሊሲም በላይ የውሃ ብክነት ስለሆነ ጄሪካኑንም ቢሆን በደንብ ማጥበቅ ፤ ቧንቧዉን አጥብቆ መዝጋት ከእናንተ ይጠበቃል ።” ካሉ በኋላ ወደ አጀንዳ ሁለት ለመግባት ማንንም አላይም ፣ አልሰማም ብለው ወረቀታቸው ላይ ተቀረቀሩ ። ይሁን እንጂ አንድ ሙሉ ልጅነቱን አቁማዳ ውስጥ ያሳለፈ የሚመስል ወጠምሻ ድምፁን ከፍ አድርጎ ማንባረቅ ጀመረ፤
“ክቡር ከንቲባችን!”
እድምተኛው በሙሉ በትዝብት አፈጠጠበት ።
“ክቡር ከንቲባችን! እንዴት ነው ፍሰት በቤት ውስጥ ይሁን የምትሉት? እኛ ኳስ ሜዳ ሄደን እንጫወታለን ። ለምሳሌ እሁድ እሁድ ከጠዋት ከ ፩ እስክ ፫ - ፬ ሠዐት ፍልሚያ ነው ። ብርም ይመደብበታል ። ከተፋለምን በኋላ የአንዳንዶቻችን ቤት ሩቅ ስለሆነ ትንሽ ውሀ ከሠፈር ለማምነን ፤ ሜዳው ዳር ለቅለቅ ብለን ነው የምንበተነው ። እንዴት ነው ታዲያ ፍሰት ይቁም የሚሉት? የኛስ ኳስ?”
ከንቲባው የታዳሚው የፍሰት አባዜ በቀላሉ የማይፈታ መሆኑ ገብቷቸው ፤ ሩብ ላይ የተውትን ውሃ ተጎንጭተው ፤ ተስፋ በቆረጠ አንደበት ፣
“እነዚህን ሁሉ ጥያቄዎች በአካባቢያቹ ባሉት ቀበሌ ጽ/ቤቶች የሚስተናገዱ ይሆናል ። ልክ ነው ፤ የሁሉም ነዋሪ ህይወት በቀመር ይለያያል ። የምናወጣው ፓሊሲ የጋራ እንደመሆኑ መጠን የሚያስከትለው ተጽዕኖ አዳመጦ መልስ መስጠት የኛ ድርሻ ነው ። ስብሰባው ወደ ፊት እንዲሄድ እና ያልዳሰስናቸዉን ነጥቦች እንድናስተናግድ ለአሁን በቀበሌ ቅሬታችሁን አስመዝግቡ።”
○●
በወሩ ከንቲባው ከስብሰባው ቀሩ ። እንጥላቸው ወርዷል ተባለ ፡፡
“ለምን ወረደ? እናንተ አትንከቧከቧቸውም እንዴ?” በማለት እድምኞቹ በቁጣ እየተንጫጩ እና እየተራገሙ ስብሰባው ሳይጀመር ጥለውት ሄዱ ።
ከንቲባውም የሆነውን ሲሰሙ ፣ ከእንጥል መውረድ ወደ ድካም ፣ ከድካም ወደ ንጭንጭ ፣ ከንጭንጭ ወደ እርጅና ተሻግረው ፤ እድሜቸው ሳያጥር አጥሮ ፤ የሠፈሩ መንገዶች ውሃ ለዕለት ሳያጡ ፤ የሀገሬው ህዝብ በነቂስ ወቶ ፤ እሪታ እና ዋይታ በተደበላለቀበት ቀትር ፣ ከደረቅ መሬት ተቀበሩ።●
በቦስተን ክ/ሀገር፣ የተአመ፣ ሐምሌ ፳፻፲፩ ተጻፈ
